መጋቢ ታምራት ኃይሌ ኢየሱስ ክርስቶስን የግል አዳኝና ጌታው አድርጎ የተቀበለው በኦርቶዶክስ ተሀድሶ በቀድሞ አጠራሩ ኃይማኖተ አበው ተብሎ ይጠራ በነበረው የወጣቶች እንቅስቃሴ ውስጥ ሲሆን ይኸው እንቅስቃሴ በወቅቱ ከእናት ቤተክርስቲያን በደረሰበት ትጽዕኖና ስደት ምክኒያት ሲዳከም በአቅራቢያው ይገኝ ወደ ነበረው የብርሃነ ወንጌል መጥምቃውያን ቤተክርስቲያን በመሔድና የውሀ ጥምቀት ሥርዓት በመፈጸም የቤተክርስቲያኒቱ አበል ሆነ።
መጋቢ ታምራት ኃይሌ በብርሃነ ወንጌል መጥምቃዊት ቤተክርስቲያን የ “ሀ” መዘምራን ውስጥ ለ8 ዓመታት አገልግሎአል። በተጨማሪ በዚህቹ ቤተክርስቲያን ውስጥ በመጽሐፍ ቅዱስ አስጠኚነት፣በጸሎት አገልግሎት አስተባባሪነት፣በወንጌል ሥርጭት ቡድን አባልነት፣በወርሀዊ የጥሞና መጽሔት ተባባሪ አዘጋጅነት፣በአምልኮ መሪነትና በሶሎ መዝሙር ፣ወደመጨረሻ ላይም የእግዚአብሔርን ቃል በማካፈል እያገለገለ እያለ በወቅቱ በተነሳው አገር አቀፍ የወንጌላውያን አማኞች ስደት ምክኒያት ጸሎት ቤቱ ሲዘጋ አባልነቱን ወደ መሠረተ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን በመዛወር በአገልግሎት ምክንያት ወደ ሰሜን አሜሪካ እስከመጣበት ወቅት ድረስ በልዩ ልዩ መስክና ደረጃ ሲያገለግል ቆይቶአል።
በመሠረተ ክርስቶስ ቤተክርስቲያንም በረዳት ወንጌላዊነትና በወንጌላዊነት፣በተለይም የአዲስ አበባዋ አጥቢያ ተዘግታ የቤት ለቤት አገልግሎት ሲደራጅ በሁሉም የከተማይቱ ክፍሎች በመዘዋወር በቤት ኅብረቶች ቃሉን በማስተማርና በማስጠናት፣የጸሎትና የአምልኮ ፕሮግራሞችን በማስተባበር፣አዳዲስ አማኞችን ክትትል ትምህርት አስተምሮ በማጥመቅ፣የአገልግሎት ሥልጠናዎችን በመስጠት፣በተለይም በደቡብ አዲስ አበባ የተመሠረተችውን የ”ቴሌ ቡልጋሪያ” አጥቢያን ከቤት ውስጥ ኅብረት ጀምሮ በማዋቀርና የመሪዎችን ኮሚቴ መሥርቶና ራሱም የኮሚቴው አባልና ሰብሳቢ በመሆን ኅብረቱ ወደ አጥቢያነት እንዲያድግ ድጋፍ አድርጓል።
ከዚያም በመሪዎች ውሳኔ ወደ መሐል አዲስ አበባ ተዛውሮ በወንጌላዊነት፣በረዳት መጋቢነትና በዋና መጋቢነት በድምሩ ለ11 ዓመታት አገልግሎአል። በነዚሁ ዓመታትም ከአጥቢያዋ ሌላ በአዲስ አበባ ክልል መሠረተ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን የወንጌል ሥርጭትና ቤተክርስቲያን ምሥረታ ኮሚቴ አባልና ጸሐፊ፣የክልሉ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ኅብረት ሰብሳቢ፣የክልሉ ሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ አባልና ጸሐፊ በመሆን አገልግሎአል።ከዚህ ሌላ በኢትዮጵያ መሠረተ ክርስቶስ ቤተክርስቲያን የአገር አቀፉ እረኝነት ኮሚቴ አባል፣እንደዚሁም የአገር አቀፉ ሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ አባልና ጸሐፊ በመሆን አገልግሎአል።
መጋቢ ታምራት ኃይሌ በዋናነት በሚታወቅበት የዝማሬ አገልግሎቱ በመላ ኢትዮጵያ በተዘረጉ የወንጌላውያን አብያተክርስቲያናት አጥቢያዎችና ዋና ጽሕፈት ቤቶች እንደዚሁም መንግሥታዊ ያልሆኑ ክርስቲያናዊ የዕርዳታ ድርጅቶች ውስጥ በኮንፈረንሶች፣በሥልጠናዎችና መደበኛ የአምልኮ ፕሮግራሞች ሁሉ ቃሉን በመስበክና በማስተማር እንደዚሁም በዝማሬና አምልኮ ሲያገለግል ኖሮአል።
መጋቢ ታምራት ኃይሌ የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖ ወደ አሜሪካን አገር ሳክራሜንቶ ከተማ ከመጣ በኋላ በቀድሞ ሥምዋ “የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ኅብረት ቤተክርስቲያን በሣክራሜንቶ” በአሁንዋ ቤቴል ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን በሣክራሜንቶ በዋና መጋቢነት እያገለገለ ሲሆን፣ከዚህ ከሣክራሜንቶ ከተማ በመነሣት በመላ የዩናይትድ ስቴትስ ከተማዎች፣እንደዚሁም በካናዳ፣በአውሮፓና በደቡብ አፍሪካ ከተማዎች፣በተጨማሪም በአረብ አገራት እየተዘዋወረ ወንጌልን በማገልግል ላይ ይገኛል። የአገልግሎቱ ዋና ትኩረትም “በደቀመዝሙርነት የሕይወት (የባሕሪ) ግንባታ የቤተክርስቲያንን ተሐድሶ ማፋጠን”፣ እንደዚሁም “የምትነጠቅን ቤተክርስቲያን ለሙሽራዋ ማዘጋጀት” የሚል ነው። ትምህርቶቹም ሆኑ ዝማሬዎቹ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ የተቃኙ ናቸው።
መጋቢ ታምራት ኃይሌ በመድረክ ከሚያቀርበው አገልግሎት ሌላ ልዩ ልዩ ርዕሶችን የሚዳስሱ ዝማሬዎቹን በ 13 አልበሞች (CDs) ለሕዝበ ክርስቲያኑ አቅርቦአል። እነኚህን ዝማሬዎች በሙሉ የያዘ የመዝሙር መጽሐፍም ለሕዝብ ያቀረበ ሲሆን ጠቅላላ የሕይወት ታሪኩን (Biography) እና የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያናት በስደት (በአብዮቱ) ዓመታት በምን ዓይነት መንገድ እንዳለፈችና እንደተባዛችም የሚተነትን ትልቅ መጽሐፍ ጽፎ በማቅረብ ለሕዝብ በረከት እንዲሆን አድርጓል።
መጋቢ ታምራት ኃይሌ በትምህርት ረገድ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱ በኋላ በተግባረ ዕድ የሙያና የቴክኒክ ትምህርት ቤት በኤሌክትሪክ በዲፕሎማ የተመረቀ ሲሆን እዚህ ዩናይተድ ስቴትስ ከመጣ በኋላ ከኤፒክ ባይብል ኮሌጅ (Trinity life Bible College) በፓስቶራል ሊደርሺፕ ሜጀር ብባችለርስ ዲግሪ ተመርቋል።
መጋቢ ታምራት ኃይሌ ከባለቤቱ ወይዘሮ ጽጌ ረታ ጎበና እንደዚሁም ከልጆቻቸው ዳግማዊ ታምራት፣ወንጌል ታምራት፣ኢያሱ ታምራትና ካሌብ ታምራት ጋር በሣክራሜንቶ፣ካሊፎርኒያ ይኖራል።